አሜሪካ በባሕረ ሰላጤው ላይ ጥቃት መፈፀሟን ስትገልጽ ኢራን የአጸፋ ምላሽ ሰጠሁ አለች

በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚያልፉ ሁለት መርከቦች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ እና ኢራን ድርድር እያደረጉ ቢሆንም የሆርሙዝ ወሽመጥ አሁንም እንደተዘጋ ነው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በሳምንቱ መጨረሻ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተኩስ ልውውጥ መካሄዱ ሲገለጽ ሁለቱም በሆርሙዝ ወሽመጥ አቅራቢያ የሚገኙ ዒላማዎችን መምታታቸውን ተናገሩ።

የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) "የኢራን ራዳር እና ማዘዣ እንዲሁም በጎሩክ እና ቄሸም ደሴቶች የሚገኙ የድሮን መቆጣጠሪያዎች በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ራስን የመከላከል ጥቃት" መፈጸሙን አስታውቋል።

ይህ በእንዲህ አንዳለ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የአሜሪካ ጦር ሠፈር ላይ የአጸፋ ምላሽ ጥቃት መፈጸሙን ያስታወቀ ሲሆን የት እንደሆነ ግን ስፍራውን አልገለጸም።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀደም ብሎ የሰላም ዕቅዱን ማረም እንደሚፈልጉ ተናግረው የነበረ ቢሆንም ከኢራን ጋር "በትክክል ለመስማማት እንፈልጋለን" ሲሉ ተናግረዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረገው የሰላም ንግግር እስካሁን ድረስ ፍሬ አልባ ሲሆን ግጭቶችም ቀጥለዋል።

ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ የሰላም እቅዱን ዲሞክራቶች፣ አፈንጋጭ ሪፐብሊካኖች፣ እንዲሁም "የፖለቲካ ሸፍጠኞች" እንዲዘገይ ምክር እየሰጡ ነው ሲሉ ከስሰዋል።

ፕሬዚዳንቱ "ዘና ብላችሁ ተቀመጡ፤ በስተመጨረሻ መሳካቱ አይቀርም፤ ይሳካል" ሲለ ጽፈዋል።

የአሜሪካ ጦር ጥቃቱን የፈጸመው "በኢራን ጠብ አጫሪ ድርጊት [ቴህራን] ዩኤስ ኤም ኪው-1 ድሮንን በዓለም አቀፍ ውሃ ላይ እየበረረ መትታ መጣሏን ተከትሎ" ቅዳሜ እና እሁድ መሆኑን አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሴንትኮም በኤክስ ገጹ ላይ ባጋራው ጽሑፍ የአሜሪካ ተዋጊዎች የኢራንን አየር መከላከያዎች፣ ከምድር መቆጣጠሪዎች እና "በቀጣናው የውሃ ክልል ላይ በሚያልፉ መርከቦች ላይ ግልጽ አደጋን የደቀኑ" ሁለት ድሮኖች" መደብደቡን አስታውቋል።

ጦሩ አክሎም የአሜሪካ ወታደሮች ላይ ጉዳት አለመድረሱን አስታውቋል።

የኢራን አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ የአሜሪካ ጦር በሲሪ ደሴት የሚገኘው የግንኙነት ማማ ላይ ጥቃት ለመፈጸም የምትጠቀምበትን የጦር ሰፈር ማጥቃቱን አስታውቋል።

የኢራን ጦር በፋርስ ዜና በኩል ባስተላለፈው መልዕክት የአሜሪካ ጥቃት "የሚደገም" ከሆነ የሚወስደው ምላሽ "ሙሉ በሙሉ የተለየ" እንደሚሆን አስጠንቅቋል።

የኩዌት ጦር ከኢራን የተወነጨፉ ድሮኖች እና ሚሳዔሎችን መመከቱን የገለጸ ሲሆን ነገር ግን በየት በኩል የተወነጨፉ መሆናቸውን አላስታወቀም።

ባለፈው ሳምንት ቴህራን የአሜሪካ አየር ድብደባ ተከትሎ በኩዌት የሚገኝ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

በሚያዚያ ወር መጀመርያ ላይ በሁለቱ አገራት መካከል የተኩስ አቁም ከተደረሰ ወዲህ ዶናልድ ትራምፕ በሁለቱ አገራት መካከል ስምምነት ሊደረስ መሆኑን ቢናገሩም በይፋ ግን የታየ ነገር የለም።

በስምምነቱ ላይ የተሰማው የአሁኑ ለውጥ የማድረግ ፍላጎት በመጀመሪያ አክሲዮስ በተባለው የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የተዘገበ ሲሆን፤ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በ60 ቀናት ማራዘም፣ የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም የመክፈት ጥሪ እና በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ላይ ድርድር ማድረግ የሚያስችል ማዕቀፎችን ያካትታል።

በሆርሙዝ በኩል አንድ አምስተኛ የዓለም ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ የሚያልፍ ሲሆን ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ የመርከቦች እንቅስቀቃሴ በመስተጓጉሉ የዓለም ነዳጅ ዘይት ዋጋ አሻቅቧል።

እሁድ ዕለት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሦት ወራት በፊት የተጀመረውን የአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ለመቋጨት የሚያስችለውን ስምምነት ለማስተካከል ፍላጎት እንዳላቸው መናገራቸው ተዘግቧል።