በሰሜን ኢትዮጵያ በፌደራል ኃይሎች እና በትግራይ ታጣቂዎች መካከል ግጭት መቀስቀሱ ተገለጸ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ለወራት በውጥረት ውስጥ በቆየው የትግራይ ክልል ውስጥ ግጭት መቀስቀሱን የህወሓት እና የፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት ገለጹ።

በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት መካከል ጦርነት መቀስቀሱ የተገለጸው ረቡዕ መስከረም 13/2019 ዓ. ም. ማለዳ የትግራይ ኃይሎች መቀለ የሚገኘውን አውሮፕላን ማረፊያ ተቆጣጥረው በረራዎች መቋረጣቸው ከተነገረ በኋላ ነው።

የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን እና የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባጋሩት ጽሑፍ የህወሓት ኃይሎች ጦርነት መክፈታቸውን ገልጸዋል።

ትግራይን የሚያስተዳድሩት የህወሓት መሪዎች በበኩላቸው ባወጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተከፈተብን ያሉትን ጥቃት ለመከላከል ኃይሎቻቸው እርምጃ እንዲወስዱ መታዘዛቸውን ገልጸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪው አቶ ጌታቸው እንዳሉት "በትግራይ ሌላ ዙር ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ብዙዎች ጥረት ቢያደርጉም፣ ዛሬ ጠዋት የህወሓት አመራር" ጦርነት መክፈቱን አመለክተዋል።

አክለውም የህወሓት ኃይሎች በአፋር እና በአማራ ክልሎች በሚገኙ ቦታዎች በኩል ሙሉ ጥቃት መክፈታቸውን በመግለጽ ጦርነት መቀስቀሱ "እጅግ የሚያሳዝን" ክስተት ነው ብለዋል።

የህወሓት መሪዎች በበኩላቸው ኃይሎቻቸው ወደ መከላከል ውጊያ እርምጃ መግባታቸውን ገልጸው፤ ውሳኔው የተላለፈው የመንግሥት ኃይሎች ቀደም ብለው ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ነው ሲሉ ከስሰዋል።

የህወሓት አመራሮች የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥትን በማፍረስ ሥልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብተው የቆዩ ሲሆን፣ አልፎ አልፎም ግጭቶች ሲከሰቱ ነበር።

በተጨማሪም ባለፉት ወራት በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች የህወሓት ኃይሎችን ዒላማ ያደረጉ ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃቶች ሲፈጸሙ እንደነበረ ሲዘገብ ቆይቷል።

ውጥረቱ ወደ ቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭት የተሸጋገረው የትግራይ ኃይሎች የመቀለውን አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያን ተቆጥጥረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ትግራይ የሚደረጉ በረራዎችን ማቋረጡን ካስታወቀ በኋላ ነው።

የትግራይ ኃይሎች ግጭቱን መቀስቀሳቸውን በኤክስ ገጻቸው ላይ ያመለከቱት አቶ ጌታቸው "የህወሓት የፖለቲካ እና የወታደራዊ አመራር ኃላፊነት የጎደለው አካሄድ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን" ጠቅሰዋል።

ግጭት መቀስቀሱን በተመለከተ ከፌደራል መንግሥቱ ይፋዊ የሆነ መግለጫ እስካሁን አልተሰጠም።

የአፋር ክልል ኮምንኬሽን ቢሮ ዛሬ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ ህወሓት "ከዛሬ ሌሊት ጀምሮ በአፋር ክልል ኪልበቲ ረሱ ዞን በአብአላ፣ በመጋሌ፣ በወሰማና በሌሎች አካባቢዎች" ላይ ጦርነት "መክፈቱን" ገልጿል።

የክልሉ መንግሥት "የሕዝቦቹን ደኅንነት እና ሰላም ለመጠበቅ" ሲልም "ከሌሎች ወዳጅ ኃይሎች ጋር በመሆን አጸፋዊ ራስን የመከላከል እርምጃ" እንደሚወስድም በመግለጫው ተመልክቷል።

ህወሓት፣ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን ጨምሮ ሰባት ታጣቂ ቡድኖች በጥምረት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን መንግሥት በማስወገድ "በሽግግር ቻርተር የሚመራ አካታች የሽግግር መንግሥት" የመመሥረት ዓላማ እንዳላቸው ይፋ ያደረጉት ከቀናት በፊት ነበር።

'የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለሕልውና' የተባለው ይህ ጥምረት ዛሬ ባወጣው መግለጫ "በአየር እና በምድር መጠነ ሰፊ ጥቃቶች" እንደተከፈቱ ገልጿል። "የብልጽግና አገዛዝ" ከፍቶታል ካለው ጥቃት በተጨማሪ "በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሕዝብ አገልግሎቶችንም ጭምር አቋርጧል" ሲል ከስሷል።

የጥምረቱ አባል ድርጅቶች "በተለይ በሰሜን ወሎ፣ በዋግሕምራ፣ በአፋር ክልል ሰሜናዊ ቀጠናዎች" ላይ "ፀረ ማጥቃት" እያደረጉ እንደሆነ በመግለጫው ጠቅሷል።

ከዚህ ቀደም የህወሓት መሪዎች የፌደራል መንግሥቱን "የመጣል ዓላማ" እንዳላቸው ሲገልጹ የነበሩ ሲሆን፤ ባለለፉት ወራትም የፌደራል መንግሥቱ የትግራይ ኃይሎችን ዒላማ ያደረጉ ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃቶችን ሲያደርስ ቆይቷል።

ደም አፋሳሹ የትግራይ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ከተገታ በኋላ የስምምነቱ ተፈጻሚነት ላይ የፌደራል መንግሥቱም የትግራይ አመራሮችም ጥያቄ ሲያነሱ ቆይተዋል። ለተፈጠሩ ክፍተቶች አንዳቸው ሌላቸውን ሲወቅሱም ነበር።

የፕሪቶሪያ ስምምነት አሸማጋይ በሆኑት የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ አማካኝነት የፌደራል መንግሥት እና የህወሓት አመራሮችን ለማሸማገል የሚደርገው ጥረት እንዲቀጥል ምዕራባውያን አገራት ማሳሰባቸው አይዘነጋም።