ህወሓት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆን "ገለልተኛ አይደሉም" ማለቱ አንድምታው ምንድን ነው?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ህወሓት የፕሪቶሪያ ስምምነት አሸማጋይ የሆኑት የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ "የገለልተኛ አደራዳሪነት መርኅ አልታየባቸውም" ሲል ከስሷል።

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆ ለቀረበባቸው ክስ በጽሕፈት ቤታቸው በኩል በሰጡት ምላሽ፤ በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ባለሥልጣናት መካከል የነበረው ግንኙነት ተቋርጦ የፕሪቶሪያን ስምምነት የሚጥሱ ሙከራዎች እንዲሁም "ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ጠብ ጫሪ" ሁኔታዎች በመታየታቸው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንደጀመሩ አስታውቀዋል።

የትግራይ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ከተገታ በኋላ የስምምነቱ ተፈጻሚነት ላይ ሁለቱም ወገኖች ጥያቄ እያነሱ ሲሆን፤ ለተፈጠሩ ክፍተቶች አንዳቸው ሌላቸውን ሲወቅሱም ይደመጣል።

በስምምነቱ መሠረት መፈጸም የነበረባቸው በርካታ ጉዳዮች ተግባራዊ አለመሆናቸውን ሁለቱም ወገኖች ሲያነሱ ቆይተዋል።

በትግራይ ክልል ባለሥልጣናት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የተባባሰው መካረር ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋትም አጭሯል።

ባለፉት ሳምንታት በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የድሮን ጥቃቶች መፈጸማቸው ተዘግቧል።

የአፍሪካ ኅብረት የፌደራል መንግሥት እና የህወሓት አመራሮችን ለማሸማገል የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ የአውሮፓ ኅብረት አባል የሆኑ የ22 አገራት እንዲሁም የዩናይትድ ኪንግደም፣ ኖርዌይ እና ካናዳ ኤምባሲዎች ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ኦባሳንጆ ነሐሴ 18/2018 ዓ. ም. በትግራይ "ድንገተኛ ጉብኝት" ማድረጋቸውን የክልሉ አስተዳደር ማስታወቁን ተከትሎ ነው ምዕራባውያኑ አገራት መግለጫ ያወጡት።

ከዚህ ጉብኝት ከሁለት ወራት በፊት ሰኔ ላይ ኦባሳንጆ ወደ መቀለ ተጉዘው እንደነበር አይዘነጋም።

የትግራይ ክልል አስተዳደር ከፌደራል መንግሥት ጋር ውይይት ለመጀመር "መሠረታዊ እና ቁልፍ" ናቸው ያላቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ማስቀመጡን አስታውቋል።

ያለፈው እሑድ በወጣው መግለጫ ግን "በቅርቡ... በኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በኩል የማደራደሩ ሂደት እንደገና ሊጀመር መሆኑን የሚያመለክት የይምሰል ድራማዎች ለመፍጠር የተደረገ ጥረት ታይቷል" በማለት እንቅስቃሴው "በራሳቸው ተነሳሽነት ወይስ በብልፅግና ትዕዛዝ ነው የሚል ከባድ ጥያቄን እያስነሳ ይገኛል" ብሏል።

ኦባሳንጆ የጀመሩት የማሸማገል ጥረት የትግራይ ባለሥልጣናት የገለልተኛነት ጥያቄ እስካነሱበት ወቅት ድረስ "በተሳካ ሁኔታ ሲካሄድ እንደነበር" ኦባሳንጆ በጽህፈት ቤታቸው በኩል ባወጡት መግለጫ ገልጸለል።

ኦባሳንጆ ላይ የተነሳው "የገለልተኛነት" ጥያቄ

የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት እና የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል አሰፋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ አሸማጋይ አካላት ጦርነት ውስጥ ካሉ አካላት ነጻ በሆነ መልኩ ማሸማገል ቢኖርባቸውም አሁን ባለው ሁኔታ በአፍሪካ ኅብረት ተወክለው በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ መካከል እንቅስቃሴ ለመምራት ውክልና የተሰጣቸው ኦባሳንጆ "ከውግን እና ነጻ ናቸው" ብለው አያምኑም።

"ሰኔ ላይ መጥተው በአንድ ወይም በሁለት ሳምንት እመለሳለሁ ብለው ነበር፤ ነገር ሁለት ወር ቆይተዋል" ብለዋል።

ለምን በቃላቸው መሠረት አልተመለሱም ሲባል የፌደራል መንግሥት ብሔራዊ ምክክር እስከሚያልቅ "ወደ ትራግራይ እንዳትሄድ ብሎኛል" የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ጠቅሰዋል።

"ሰላማዊ ሁኔታ እንዲፈጠር ከተፈለገ በምንም መልኩ ውግንና የሌለው መሆን አለበት የሚል ሐሳብ ነው ያለን" ብለዋል።

ኦባሳንጆ ለዚህ በሰጡት ምላሽ በማሸማገል ሒደታቸው ከፌደራል መንግሥቱ "ትዕዛዝ እንደማይቀበሉ" ገልጸዋል።

አቶ አማኑኤል "ሰላማዊ ሁኔታ የሚፈለግ ከሆነ፣ ውይይት የሚፈለግ ከሆነ የእሳቸው አካሄድ አግባብነት የለውም" ሲሉ የክልሉን መንግሥት አቋም ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ኦባሳንጆ ትግራይ ሳሉ የተሰጧቸው ነጥቦች ላይ "ከፌደራል መንግሥት ጋር ተነጋግሬ እመጣለሁ" ማለታቸውን ጠቅሰው "በእነዚያ ነጥቦች ላይ የሚጨበጥ ነገር ይዘው አልመጡም" ብለዋል።

ይሄ አካሄድ "ለዘላቂ ሰላም ጥቅም የለውም" ያሉት አቶ አማኑኤል፤ ሌሎች ዓለም አቀፍ አካላት የሚደግፉት እና የተሻለ ውጤት ሊያመጣ የሚችል "ሐቀኛነት ድርድር" መደረግ እንዳለበት ገልጸዋል።

ኦባሳንጆ በበኩላቸው ለአንድ ወገን "ያደላሉ" የሚለው ክስ እስካሁን ያከናወኑትን ጥረት እና ውክልናቸውን "የሚያዛባ" መሆኑን በመግለጫቸው ተናግረዋል።

አቶ አማኑኤል በበኩላቸው ድርድር መከናወን ያለበት "ምንም ውግንና በሌለው፣ ነጻ ሆኖ ሁሉንም አካል በሰላማዊ መንገድ ማደራደር የሚችል አካል ነው" ብለዋል።

"የፕሪቶርያ ስምምነት ነጥቦች መሬት ወርደው እንዲተገበር አደራዳሪዎች የሚገባቸውን ጫና አላደረጉም" በማለትም ኦባሳንጆ ላይ የሚያነሱትን ጥያቄ አብራርተዋል።

ኦባሳንጆ በሰጡት ምላሽ በኢትዮጵያ ለሚካሄደው የሰላም ጥረት "ቁርጠኛ" አቋም እንዳቸው እንዲሁም ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በአፍሪካ ኅብረት የሚመራው የሰላም ጥረት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የገለልተኛነት ጥያቄ መነሳቱ አንድምታው ምንድን ነው?

በሰላም ግንባታ፣ በግጭት አፈታት እና በዓለም አቀፍ ሕግ ዙሪያ ለብዙ ዓመታት የሠሩት የሕግ ባለሙያ እና ከፍተኛ ተንታኝ አቶ ባይሳ ዋቅወያ በህወሓት የወጣው መግለጫ "ያልተጠበቀ ነው" ብለዋል።

በግለሰብ ደረጃ እና የአፍሪካ ኅብረትን በመወከልም "ጊዜያቸውን የሰውት ግለሰብ በእሳቸው ላይ አመኔታ የለንም፣ በአንደኛው ተደራዳሪ ወገን ተጽዕኖ ሥር ናቸው መባሉ ያሳዝናል" ብለዋል።

ሆኖም ግን አንደኛው ተደራዳሪ ወገን በአደራዳሪዎች ላይ ጥርጣሬ ማንሳቱ በዲፕሎማሲው ዓለም የተለመደ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

ኦባሳንጆ ከህወሓት ለቀረበባቸወ ወቀሳ በሰጡት ምላሽ "በአንድ ግጭት ውስጥ የቀረቡ ፍላጎቶች ተቀባይነት ካላገኙ ወይም አንድ ወገን የሚጠብቀው ካልተሳካ መፍትሄው አደራዳሪውን ማጥቃት ወይም አቋሙን ጥያቄ ውስጥ መክተት ሳይሆን፣ አስማሚ ነጥብ ላይ እስኪደረስ ንግግርን መቀጠል ነው" ብለዋል።

አቶ ባይሳ "ኦባሳንጆ ተዓማኒት ያገኙ ቢመስልም አልሆነም። በሁለቱም በኩል የሰላም ሒደቱ እንዲቀጥል የሚፈለግ ይመስለኛል። ጥሩ ነገሩ እና በጣም ደስ የሚለው [ኦባሳንጆ ላይ] እምነት የለንም እንጂ ድርድሩን አንፈልግም አለማለታቸው ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።

በድርድር ሒደቱ ላይ ጥያቄ አለመነሳቱ "ተስፋ እንደሚሰጥ" ጠቅሰው ለሁለቱም ወገኖች የሚቀርብ አደራዳሪ መፈለግ እንደሚቻል ተናግረዋል።

ከዓለም አቀፍ የድርድር ልምዳቸው ተነስተው አንድ ወገን አንድ አደራዳሪን "አልፈልም" ለማለት "ምክንያት መስጠት" እንደሌለበተወት ይናገራሉ።

በህወሓት በኩል የቀረቡት "ምክንያቶች ሳይሆኑ ሰበብ ይመስሉኛል" ሲሉም አስተያየታቸውን ለቢቢሲ ሰጥተዋል።

ነገር ግን አደራዳሪዎች ላይ በአንደኛው ወገን ጥያቄ ከተነሳ በኋላ መልሶ "በስህተት ይሆናል" በሚል ያንን አደራዳሪ መልሶ መምጣት ለድርድሩ እንደማይጠቅም ይገልጻሉ።

በተለመደው የዲፕሎማሲ አካሄድ ከዚህ በኋላ ኦባሳንጆ አደራዳሪ ሊሆኑ እንደማይችሉም የግል ምልከታቸውን ያስረዳሉ።

"ጥሩው ነገር ቅሬታቸው በኦባሳንጆ እንጂ በንግግሩ አጀንዳ አይደለም። ንግግር ይፈልጋሉ፤ ሰዎች እንዳይሞቱ ይፈልጋሉ። ትኩረቱ መሆን ያለበት በኦባሳንጆ ላይ ሳይሆን በዚህ ላይ ነው። ሚሊዮን ኦባሳንጆዎች አሉ" በማለትም ያብራራሉ።