ሁሉንም የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ለመመልከት 50 ሺህ ዶላር የተከፈላቸው ደጋፊዎች

ሁለቱ ደጋፊዎች ማሊያ ለብሰው ምግብ እየተመገቡ እና ዓለም ዋንጫን እየተመለከቱ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የዓለም ዋንጫ በየቀኑ የተደለደሉ ስድስት ጨዋታዎች እየተደረጉበት ቀጥሏል። ሁሉንም ጨዋታዎቹን መመልከት የሙሉ ሰዓት ሥራ ይሆናል።

ይህ ለኬቨን አኮቶ እና ኦስተን ፍራንክሊን እውን ነው። ሁለቱ ደጋፊዎች ሁሉንም 104 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ለመመልት እያንዳንዳቸው 50 ሺህ ዶላር ይከፈላቸዋል።

የፎክስ ዋን "የዓለም ዋንጫ ዋና ተመልካቾች" የሆኑትን ሁለቱ ተመልካቾች ከአንድ ሣምንት በላይ ሚናቸውን ሲወጡ ተሞክሯቸው ምን እንደሚመስል ቢቢሲ አነጋግሯቸዋል።

በኒው ዮርክ ታይምስ ስኩየር መሀል ላይ ቁጭ ያለውን በመስታወት የተሰራ ሳጥን አለማየት አይቻልም። በዚህ ሳጥን ውስጥ መደገፊያ ያላቸው ወንበሮች፣ ቡናማ ቀለም ያላቸው ሁለት ሶፋዎች፣ ሁለት ግዙፍ ስክሪን ያላቸው ቴሌቪዥኖች አና ጆተኒ ይገኛል።

የደጋፊዎች መመልከቻ እንዲመስልም ለሽያጭ የቀረቡ ቁሳቁሶች እና ለመቆያ የሚሆኑ ምግቦችም አሉ።

ኬቨን ለቢቢሲ "ልክ እንደ ማንኛውም የ20 ዓመት ልጅ አዕምሮ ውስጥ እንዳለው ነው፤ እዚህ ውስጥ የሆነ ነገር ማስቀመጥ ከቻልክ እንደ እግር ኳስ ደጋፊ ታስቀምጠዋለህ" ብሏል።

ፍሎሪዳ የምግብ አብሳይ የሆነው ኬቨን፤ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነው የፊሎዶልፊያው አስተን ለዚህ ሥራ በሺዎች የሚቆጠሩትን በልጠው ነው የተቀጠሩት። ሥራው እያንዳንዱን ጨዋታ መመልከት ብቻ ሳይሆን ለደጋፊዎች ይዘት መፍጠር አለባቸው።

በርካታ ሣምንታት በቀሩት ዓለም ዋንጫ ኬቨን እና ኦስተን ፍጥነታቸውን ለማመጣጠን እየሞከሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"በጣም ዝዬ ነበር፤ ኦስተንም ትንሽ ደክሞት ነበር። ስለዚህ እየሆነ ያለውን ሁሉንም ነገር ለመከተል እየተማርን ነው" ይላል ኬቨን።

ኦስተንም ይስማማል። ቀናት እርስ በእርስ ከሚደበላለቁበት የክረምት የካምፕ ልምዱ ጋር አነፃፅሮታል።

"ሙሉ በሙሉ ማራቶን ነው። በአንፃሩ ቀለል ያለ ሥራ ነው። ሶፋ ላይ ተቀምጨ እግር ኳስ አያለሁ። ይሁን እንጂ አድካሚ ሆኗል። እና ስምንት የእንቅልፍ ሰዓታትን በተቻለኝ መጠን ማግኘቴን አረጋግጣለሁ።"

ሥራው በታይምስ ስኩዌር በተሰራው የመስታዎች ሳጥን ውስጥ መተኛትን ባለማስገደዱ እድለኛ ናቸው። ስለዚህም ፈረቃቸው ሲያበቃ ለሚቀጥለው ቀን ሙሉ አቅማቸው ለመቅረብ መውጣት ይችላሉ።

ጥንዶቹ ገና ከአሁኑ ታሪካዊ ክንውኖችን መመልከት ችለዋል። የአርጀንቲናን ስጋ እየበሉ ሊዮኔል ሜሲ የዓለም ዋንጫ የሁልጊዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ክብረ ወሰንን ሲሰብር ተመልክተዋል።

የጎብኝዎች ማዕከል የሆነው አካባቢው ለዓለም ዋንጫ ጎብኝዎች ሳቢ ሆኗል። የኖርዌይ ደጋፊዎች ታዋቂውን የቫይኪንግ የጀልባ ቀዘፋ ትዕይንት አሳይተዋል።

ከመላው ዓለም ከመጡ ደጋፊዎች ጋር መገናኘት እና ስለ እግር ኳስ፣ ባህል እና ስለ አሜሪካ ቆይታቸው ማውራት ለኦስተን ይህ ተወዳጁ ክፍል ነው።

"በጣም የሚያስደንቀው ነገር ታይምስ ስኩዌር ከሚያዩኝ ሰዎች ጋር እንደሆንኩ በተደጋጋሚ የምረሳ መሆኑ ነው። ለ10፣ 15 ደቂቃ ጨዋታ ተመስጨ እያየሁ ወደ ቀኜ ዞር ስል ኬቨንን እና በታይምስ ስኩዌር የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን አያለሁ። እናም ሙሉ ለሙሉ [ያለህበትን ቦታ] ትረሳለህ።"

ግምታቸውስ?

ኬቨን ስፔን ወርቃማውን ዋንጫ ትወስዳለች ብሏል። ሆኖም በትውልዱ ምክንያት አሜሪካ እና ጋናን ይደግፋል።

ኦስተን የኖርዌይን ማሊያ ለብሷል። በግል ምክንያት ግን አይደለም። ቡድኑ እና የማንችስተር ሲቲው አጥቂ ኧርሊንግ ሃላንድ እስካሁን ባሳዩት ብቃት ምክንያት ነው።

"በቀላሉ መምረጥ ይቻላል ብዬ አስባለሁ። ስፔን ወይም ፈረንሳይ ያሸንፋሉ። ኖርዌይም በትክክለኛው መንገድ ላይ ናት ብዬ አስባለሁ። ነገሮች በቦታቸው ቢሰምሩ ቤታቸው እንደሚያመጡት በደንብ ይታየኛል።"

ተመልካቾች ይህን ሥራ መፈለግ ላይ ግን የተከፋፈለ እይታ አላቸው።

የኖርዌይ ደጋፊ የሆነው የ50 ዓመቱ ኢሙንድ ሊላንድ እና የ15 ዓመት ልጁ ካሚላ ያለምንም ግላዊነት ሁሉንም 104 ጨዋታዎች መመልከት ከአቅም በላይ ነው ብለው ያምናሉ።

የ18 ዓመቱ ማቲው ሜንዴዝ ለቢቢሲ ዓለም ዋንጫን ለማየት ከጓደኞች እና ቤተሰብ ጋር ጊዜ ማሳለፉ የተሻለ መንገድ ነው ይላል።

ይሁን እንጂ የ20 ዓመቱ ሚጌል ሳንቼዝ ምን ያህል እድለኛ እንደሆኑ ማመን አይችልም።

"ምን? ዓለም ዋንጫን ለማየት መከፈል በአካል ከመሄድ እንደውም የተሻለ ነው። እብደት ነው፤ በጣም እብደት ነው።"