ዩናይትድ ኪንግደም ጥገኝነት ጠያቂዎችን የምትቀበልበት አዲስ አሠራር ልትጀምር ነው

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የዩናይትድ ኪንግደም የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ለጥገኝነት ጠያቂዎች የካናዳ ዓይነት አዲስ "የተገደበ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ሕጋዊ" መንገዶችን ከወራት በኋላ ይፋ እንደሚያደርግ አስታወቀ።
አዲሱ አሠራር ዩኒቨርሲቲዎች፣ የማኅበረሰብ ቡድኖች እና የንግድ ተቋማትን የመሳሰሉ ድርጅቶች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ለመግባት የሚያመለክቱ ስደተኞችን ስፖንሰር እንዲያደርጉ ይፈቅዳል። ይህ አሰራር የካናዳን የጥገኝነት ሥርዓት መሠረት ያደረገ ነው።
በሕገወጥ መንገድ እየገቡ ያሉትን ስደተኞች ለመቆጣጠር ጥረት በሚደረግበት ጊዜ አዲስ አሠራር መጀመሩን በተመለከተ፤ የወግ አጥባቂ ፓርቲ አባላት ሕገወጥ ስደት እስኪቆም ድረስ ተጨማሪ ሰዎች ወደ አገሪቱ መግባት የለባቸውም በማለት እየተከራከሩ ነው።
የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሻባና ማህሙድ እንደተናገሩት አዲሱ ሥርዓት "ሀቀኛ ስደተኞችን" የሚጠብቅ ሲሆን፣ "ብዙ ጊዜ አላግባብ ጥቅም ላይ የሚውሉ ክፍተቶችን ደግሞ የሚዘጋ" ነው።
ሚኒስትሯ "ብሪታንያ ሁልጊዜም ከጦርነት እና ከስደት ለሚሸሹ ሰዎች መጠጊያ ትሰጣለች። ነገር ግን ይህ ሥርዓት የሚቆየው ሕዝቡ ፍትሐዊ፣ ቁጥጥር እንደሚደረግበት እና አላግባብ ጥቅም ላይ ለመዋል ክፍት እንዳልሆነ ካመነ ብቻ ነው" ብለዋል።
አዲሱ አሠራርን በተመለከተ ዜናው የተሰማው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ የኢሚግሬሽን ረቂቅ ሕግን ለታችኛው ምክር ቤት ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ባሉበት ጊዜ ሲሆን አንዳንድ የሌበር ፓርቲ አባላት ሊቃወሙት ይችላሉ እየተባለ ነው።
በዩኬ ውስጥ በአገሪቱ ስደተኞችን መልሶ በማስፈር መርሃ ግብር ስር ስፖንሰር የሚደረጉ በአንጻራዊ ሁኔታ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ይገኛሉ። "አብዛኞቹ" ስደተኞች ግን በአካባቢ ምክር ቤቶች ድጋፍ የተደረገላቸው መሆናቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
መንግሥት በግብር ከፋዮች ወጪ በሆቴሎች ውስጥ የሚቀመጡ ስደተኞችን ቁጥር እንዲቀንስ ጫና ሲደረግበት የቆየ ሲሆን፣ አሁንም ስደተኞች በሕገወጥ መንገድ በትናንሽ ጀልባዎች ወደ አገሪቱ መምጣት መቀጠላቸው ሕዝቡ የጥገኝነት ሥርዓቱን እንዲጠራጠር አድርጎታል።
አዲሶቹ የጥገኝነት ጥያቄ አሠራሮች "ተቀባይነት ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎችን" ጨምሮ በርከት ያሉ ድርጅቶች ስደተኞችን እንዲደግፉ ያስችላል ተብሏል።
ስደተኞች በሥራ ላይ እንዲሰማሩ የሚያደርገው አሠራር በሚቀጥለው ዓመት እንደሚጀመር የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህም አሠሪዎች ስደተኞችን ስፖንሰር እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል ሲል የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በዩኒቨርሲቲ በኩል ለሚመጡ ሰዎች የማመልከቻ ጊዜ በሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ ላይ ይከፈታል፣ በዚህ ሂደት በመጠቀም የመጀመሪያዎቹ የሚሆኑት በቀጣዩ የአውሮፓውያን ዓመት እንደሚመጡ ይጠበቃል።
መንግሥት በአዲሶቹ አሠራሮች ምን ያህል ሰዎች እንዲገቡ እንደሚፈቅድ ባይገልጽም፣ በተገደበ እና በዝቅተኛ ቁጥር ከተጀመረ በኋላ እየጨመረ እንደሚሄድ ተነግሯል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥገኝነት ጠያቂዎችን ስፖንሰር ማድረግ የሚችሉ ድርጅቶችን እንደሚቆጣጠር እና ሁሉም አመልካቾች ጥብቅ ምርመራ እንደሚደረግባቸውም አስታውቋል።
የወግ አጥባቂዎቹ ትይዩ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ክሪስ ፊሊፕ፤ በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት ስደተኞች ቁጥር ዜሮ እስኪሆን ድረስ "በሰብአዊነት ምክንያት ተጨማሪ ሰዎችን ማስገባት የለብንም" ብለዋል።
ጨምረውም እርምጃዎቹ በሕገወጥ መንገድ የሚመጡ "ጀልባዎቹን አያቆምም" በማለት የሌበር ፓርቲ አባላት የአገሪቱ "ድንበሮች ክፍት" መሆንን እንደሚደግፉ ከስሰዋል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ለጥገኝነት ፈላጊዎች አዳዲስ መንገዶችን ከመክፈቱ ጋር በተያያዘ ሐሰተኛ ጥያቄዎችን እንደሚገታ አስታውቋል።















