ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ እና ካናዳ የንግድ ጦርነት ሲቀጥል፣ አሜሪካ በርካታ የካናዳ ምርቶች እንዳይገቡ አገደች
አሜሪካ የአልኮል መጠጦችን፣ የወተት ተዋጽኦ እና ሞተር ሳይክሎችን ጨምሮ በርካታ የካናዳ ምርቶች እንዳይገቡ እግድ ጣለች።
እርምጃው የተወሰደው ካናዳ በአሜሪካ ምርቶች ላይ የጣለቻቸው አፀፋዊ ቀረጦች ተግባራዊ መሆናቸውን ተከትሎ ነው።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት በፈረሟቸው ተከታታይ ፕሬዝደንታዊ ትዕዛዞች፣ ካናዳ በአሜሪካ ላይ "አድልዎ እያደረገች ነው" ብለዋል። በካናዳ ምርቶች ላይ የጣሉት እገዳ ከመስከረም 19 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆንም ገልፀዋል።
ከትራምፕ እርምጃ አስቀድመው በተመሳሳይ ቀን የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት፣ አገራቸው ከፍተኛ የንግድ አጋሯ ከሆነችው ከአሜሪካ በመራቅ አዲስ አጋሮችን ለመፈለግ በምታደርገው ሽግግር "ዋጋ በማስከፈል" የሚፈፀም ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሁለቱም አገራት የንግድ ስምምነት ላይ ለመድረስ ፍላጎት እንዳላቸው ቢገልጹም፣ የጀመሩት ድርድር በነሐሴ መጨረሻ ከተቋረጠ በኋላ አዲስ ውይይት ለማድረግ የያዙት ቀጠሮ የለም።
ቢቢሲ የካርኒን ጽሕፈት ቤት አስተያየት ጠይቋል።
የትላንቱ የዋይት ሀውስ እገዳ በአሜሪካና ካናዳ መካከል ለወራት በቆየው የንግድ ጦርነት ውስጥ የተወሰደ አዲሱ እርምጃ ነው። ሁለቱ አገራት በታሪክ የቅርብ ወዳጅነት ያላቸው ሲሆኑ፣ አንዳቸው የሌላኛቸው ቁልፍ የንግድ አጋር ናቸው።
በአጠቃላይ፣ ካናዳ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶቿ ውስጥ ከሁለት ሶስተኛ በላይ የሚሆነው ወደ ጎረቤቷ አሜሪካ ነው የሚላኩት።
በሌላ በኩል፣ ካናዳ ከሜክሲኮ ቀጥሎ የአሜሪካ ሁለተኛዋ ትልቅ የንግድ አጋር ናት። ሆኖም ወደ አሜሪካ የምትልካቸው ምርቶች ከሜክሲኮ ይልቅ በአይነት የተለያዩ ዘርፎችን ይሸፍናሉ።
በሁለቱም በኩል ያሉ የቢዝነስ ባለቤቶች፣ በአገራቱ መካከል እየተደረገ ያለው የንግድ ጦርነት ስጋት እያሳደረባቸው መሆኑን እየገለፁ ነው። ብዙዎች የሸቀጦች ዋጋ ሊጨምር እና የተጠቃሚዎች ቁጥር ሊቀንስ እንደሚችል ይገምታሉ።
ባለፈው ወር፣ በርካታ የድርድር ሂደቶች ከተቋረጡ በኋላ፣ ዋይት ሀውስ 20 ቢሊዮን ዶላር (14.8 ቢሊዮን ፓውንድ) የሚገመቱ የካናዳ ምርቶች ላይ 50 በመቶ ቀረጥ ጥሏል።
እነዚህ ቀረጦች የካናዳን የቤት ዕቃዎች ኢንዱስትሪ፣ የወይን ምርት ዘርፍ እንዲሁም አንዳንድ የስፖርት እና የዓሣ ማጥመጃ መሣሪያዎች ንግዶችን ጎድተዋል።
ካናዳም በበኩሏ በአሜሪካ ከተጣለባት ቀረጥ ጋር እኩል የሆነ "ዶላር ለዶላር" ያለችውን የበቀል ቀረጥ ጥላለች። ቀረጥ ከተጣለባቸው የአሜሪካ ምርቶች መካከል ብረት፣ አልባሳት እና የቤት ዕቃዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ቀረጡ ከማክሰኞ እኩለ ሌሊት በኋላ ተግባራዊ ሆኗል።
ዋይት ሀውስ ማክሰኞ አዲሱን እገዳ ይፋ ሲያደርግ፣ ካናዳ ከሌሎች አገራት በሚገቡ ተመሳሳይ ምርቶች ላይ የማታደርገውን ገደብ በአሜሪካ ምርቶች ላይ በማድረግ "በአሜሪካ ንግዶች ላይ አድልዎ እያደረገች ነው" ብሏል።
አልኮል የሌለበት ቢራን ጨምሮ በአንዳንድ ምርቶች ሙሉ በሙሉ እግድ ሲጣል፣ የአይብ ዓይነቶችን እና አነስተኛ ሞተር ጀልባዎችን ጨምሮ በሌሎች ምርቶች ላይ ደግሞ የቀረጥ መጠኑ እንዲጨምር መደረጉንም ገልጿል።
ተጨማሪ የንግድ ገደቦች ሊከተሉ እንደሚችሉ ሰኞ ዕለት ፍንጭ የሰጡት ትራምፕ፣ የካናዳው አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦምባርዲየር ምርቶቹን በአሜሪካ ገበያ ላይ መሸጡን መቀጠል የሚፈልግ ከሆነ ማምረቻውን ወደ አሜሪካ ማዛወር እንዳለበት አስጠንቅቀዋል።
የቀረጥ እርምጃዎች በአሜሪካና በሌሎች አገራት መካከል ያለውን የንግድ አለመመጣጠን እንደሚቀንሱ የትራምፕ የረጅም ጊዜ እምነት ነው። ሆኖም በስፋት የተጣሉት እነዚህ ቀረጦች በርካታ የአሜሪካ አጋሮችን አስቆጥተዋል።
ትራምፕ ባለፈው ዓመት ዓለም አቀፍ የቀረጥ ዘመቻቸውን ከጀመሩ በኋላ፣ አንዳንድ ካናዳውያን የአሜሪካ ምርቶችን ላለመጠቀም ዘመቻ ጀምረዋል። በዚህም ሳቢያ እንደ አልኮል መጠጦች ያሉ የአሜሪካ ምርቶች ከአንዳንድ መደብሮች መደርደሪያዎች ላይ ተወግደዋል።