ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሜታ የሕጻናት ወሲባዊ ብዝበዛ ይዘት ያላቸው ማስታወቂያዎች ማስተላለፍ መቀጠሉን አዲስ ሪፖርት አጋለጠ
ማሳሰቢያ፡ ይህ ዘገባ ጥቃትን የሚመለከት ይዘት አለው
ሜታ ሰው ሠራሽ አስተውሎት በመጠቀም በመቶዎች የሚቆጠሩ የሕጻናት ወሲባዊ ብዝበዛ ይዘት ያላቸው ማስታወቂያዎችን ማስተላለፉን አዲስ የወጣ ሪፖርት አጋለጠ።
ክፍያ የተፈጸመባቸው ማስታወቂያዎቹ ባለፉት 10 ወራት መለቀቃቸውን መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገ የመብት ተሟጋች ቡድን ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።
እነዚህ ማስታወቂያዎች በሕንድ በስፋት ወጥተዋል። ከሁለት ወራት በፊት ሜታ የሕጻናት ወሲባዊ ብዝበዛ ይዘት ያላቸውን ማስታወቂያዎች ከኢንስታግራም እንዲያጠፋ ከሕንድ መንግሥት ማሳሰቢያ ተሰጥቶት ነበር።
የሕንድ መንግሥት ማሳሰቢያ የሰጠው የቢቢሲ አይ የምርመራ ዘገባን ተከትሎ ነው። ቢቢሲ ባደረገው ምርመራ ኢንስታግራም ላይ ክፍያ የተፈጸመባቸው የሕጻናት ወሲባዊ ብዝበዛ ይዘት ያላቸው ማስታወቂያዎች ተገኝተዋል።
የአሜሪካው ተቋም 'ቴክ ትራንስፓረንሲ ፕሮጀክት' በኢንስታግራም እና ፌስቡክ ላይ 332 የሕጻናት ወሲባዊ ብዝበዛ ይዘት ያላቸው ማስታወቂያዎች ማግኘቱን አስታውቋል።
274 የሚሆኑት ማስታወቂያዎች ነሐሴ ወር ላይ የተለቀቁ ናቸው።
ሜታ ለቢቢሲ "እውነተኛም ይሁኑ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተሠሩ እርቃንን የሚያሳዩ ወይም የሕጻናት ወሲባዊ ብዝበዛ ይዘቶችን አንታገስም" በማለት ምላሽ ሰጥቷል።
"ወንጀለኞቹ የመረጃ ማጣሪያን ለማለፍ በየጊዜው አዳዲስ ስልት ይፈልጋሉ። መረጃ የምናጣራበትን መንገድ እና የምንወስደውን እርምጃ የምናጠናክረውም ለዚህ ነው" ሲልም አክሏል።
የአውሮፓ ንጉሣውያን ቤተሰብ ልጆችን ጨምሮ በርካታ የሕጻናት ምሥሎች መገኘታቸውን ይፋ የተደረገው ሪፖርት ይጠቁማል።
እነዚህ ምሥሎች በሰው ሠራሽ አስተውሎት ተቀናብረው ማስታወቂያ ለመሥራት ውለዋል።
የመብት ተሟጋች ድርጅቱ ግኝቱን ለሜታ አጋርቷል።
በሕንድ ከተለቀቁ ማስታወቂያዎች መካከል 78 ያህሉ የወጡት የአገሪቱ መንግሥት ማስጠንቀቂያ ከሰጠ በኋላ ነው።
የሕንድ መንግሥት ከሜታ አመራሮች ጋር ተገናኝቶ የሕጻናት ወሲባዊ ብዝበዛ ይዘቶች ያሏቸው ማስታወቂያዎች እንዲቆሙ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ ከወጣ በኋላ የሕንድ ብሔራዊ ተቋማት ምርመራ እንደሚከፍቱ አስታውቀዋል።
በሕንድ የሕጻናት ወሲባዊ ብዝበዛ ይዘቶችን ማሰራጨት ወንጀል ነው። የሜታ ፖሊሲም የሕጻናት ወሲባዊ ብዝበዛ ይዘቶች ማሰራጨትን ያግዳል።
በሕንድ የሚገኙ 250 የሕጻናት መብት ላይ የሚሠሩ ተቋማት ስብስብ መሥራች ቡህዋን ሪብሁ እንደሚናገሩት፤ የቢቢሲን ዘገባ መነሻ በማድረግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፊርማ አሰባስበው አስገብተዋል።
የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች የሕጻናት ወሲባዊ ብዝበዛ ይዘቶችን እንዲለዩ አስገዳጅ ሕግ እንዲወጣ ጠይቀዋል።
"የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች የሕንድን ሕግ በግልጽ እየጣሱ ነው" ይላሉ።
ይፋ የተደረገው ሪፖርት የቴክኖሎጂ ተቋማት ተጠያቂ እንዲደረጉ ይጠይቃል።
በአሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አውሮፓ ኅብረት፣ አውስትራሊያ እና ሕንድ በኢንስታግራም እና ፌስቡክ ላይ የሕጻናት ወሲባዊ ብዝበዛ ይዘት ያላቸው 332 ማስታወቂያዎች ተገኝተዋል።
አብዛኞቹ ማስታወቂያዎች የሕጻናት ምሥል በማሳየት ይጀምራሉ። የተቀረው ቪድዮ በኤአይ ተቀናብሮ ሕጻናቱ ወሲባዊ ድርጊት ሲፈጽሙ ያሳያል።
አንዲት ታዳጊ ሴት ወሲባዊ ድርጊት ስትፈጽም የሚያሳየው ቪድዮ ላይ የሚሰማው ድምጽ "ምንም ገደብ የለም። ሁሉም ገጸ ባህሪዎች እውነተኛ ሰዎች ናቸው። ብዙ አማራጮች አሉ። ወንዶች ይሄንን ኤአይ መጠቀም ይችላሉ" ይላል።
ሐምሌ ላይ ቢቢሲ የምርመራ ዘገባ ሲያወጣ፤ ሜታ "ፖሊሲያችንን የሚጻረሩ ይዘቶችን ማንኛውም ሰው መጠቆም ይችላል" የሚል ምላሽ ሰጥቶ ነበር።
የአሜሪካው ተቋም 'ቴክ ትራንስፓረንሲ ፕሮጀክት' ከ84 ማስታወቂያዎች በ55ቱ ላይ ጥቆማ ሰጥቷል።
ሜታ 43ቱ ማስታወቂያዎች ከፖሊሲው ጋር እንደማይጋጩ ምላሽ ሰጥቷል። 11 ይዘቶችን ግን ከገጹ አጥፍቷል።
ሜታ ማስታወቂያዎች ላይ ጥቆማ የመስጠት አማራጭ ያለው በቀጥታ እየተሰራጩ ሳለ ብቻ ነው።
ሜታ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ "ፖሊሲ የሚጥሱ ይዘቶችን ማጥፋት ጨምሮ ጠንካራ መከላከያ መንገዶች ዘርግተናል። ጉዳዩን መመርመር እንቀጥላለን። ጥቆማ የተደረገባቸው ማስታወቂያዎች ተሰርዘዋል" የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
አብዛኞቹ ማስታወቂያዎች "ከ200 በላይ ምላሽ እንዳላገኙ" እና ለማስታወቂያዎቹ የተከፈለው ገንዘብም "ከ5,000 ዶላር ያነሰ" እንደሆነ ገልጿል።
በሕንድ ከፍተኛ የሳይበር ደኅንነት ባለሙያ የሆኑት ሺካ ጎል እንደሚናገሩት፤ ተጠቃሚዎች በቀላሉ ከአንድ ድረ ገጽ ወደ ሌላው መሻገራቸው የቁጥጥር ሒደትን ከባድ ያደርገዋል።
"መንግሥት ከማኅበራዊ ሚዲያ ተቋማት ጋር ሲነጋገር ይሄንን ጉዳይ አንስቶ ትዕዛዝ ይሰጣቸዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ይላሉ።
ቢቢሲ በምርመራው ያገኛቸው ማስታወቂያዎች ተጠቃሚዎችን ወደ ቴሌግራም ገጽ ይወስዳሉ። ተጠቃሚዎች ይዘቱን ከአንድ ዶላር ባነሰ መግዛትም ይችላሉ።
ቴሌግራም የሕጻናት ወሲባዊ ብዝበዛ ያላቸው ይዘቶችን ከገጹ እንደሚሰርዝ ለቢቢሲ ገልጿል።