ሆርሙዝ ወሽመጥን በመተካት ነዳጅ እና ጋዝ የሚተላለፍባቸው አማራጭ መስመሮች አሉ?

በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል በየቀኑ ወደ 20 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ እና ጋዝ ይጓጓዛል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል በየቀኑ ወደ 20 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ እና ጋዝ ይጓጓዛል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

ኢራን እና አሜሪካ ወደ ግጭት መመለሳቸው የሆርሙዝ ወሽመጥን በድጋሚ መነጋገሪያ አድርጎታል።

ለዓለም የንግድ መርከቦች ዋነኛ መተላለፊያ የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ የበርካቶችን ትኩረት ስቧል።

ኢራን እና አሜሪካ በዘላቂነት ጦርነቱን የሚያስቆም የመግባቢያ ሰነድ ቢፈራረሙም ግጭቱ ባለፉት ሳምንታት ተቀስቅሷል። በዚህም ምክንያት የነዳጅ ዋጋ ንሯል።

በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መተላለፍ ለመርከቦች አደገኛ ከሆነ የባሕረ ሰላጤው አገራት ነዳጅን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ለማስገባት ሌሎች አማራጮች አሏቸው?

ባለሙያዎች አማራጮች አሉ ቢሉም እነዚህ አማራጮች የሆርሙዝ ወሽመጥን መተካት አይችሉም።

በኢራን እና ኦማን መካከል የሚገኘው የሆርሙዝ ወሽመጥ ለባሕረ ሰላጤው አገራት ዋነኛ ነዳጅ ማጓጓዣ መስመር ነው።

የሆርሙዝ ወሽመጥ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ሰፊ መጠን ያለው የነዳጅ ምርት ማስተላልፍ የሚያስችል አማራጭ ነው።

ከነዳጅ ማመላለሻ ቱቦ አንጻር የሆርሙዝ ወሽመጥ በአነስተኛ ወጪ ከፍተኛ የነዳጅ ምርት ያስተላልፋል። የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ መሠረተ ልማት ለመዘርጋት ከሚጠይቀው ወጪ ባሻገር የጥገና ወጪውም ከፍተኛ ነው።

ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ እንደሚለው በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል በየቀኑ ወደ 20 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ እና ጋዝ ይጓጓዛል። ይህም ከዓለም የኃይል አቅርቦት ሩብ ያህሉን ይሸፍናል።

ከዚህም ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነው ነዳጅ መዳረሻው እስያ ነው። በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የዓለም አንድ አምስተኛ ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝም ይዘዋወራል።

በተለይም ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ዝውውር ሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የተመረኮዘ ነው። ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያው የሚገባው በዚህ መስመር ብቻ ስለሆነ ሌላ የመጓጓዣ አማራጭ የለውም።

ኢራን እና አሜሪካ ወደ ግጭት መመለሳቸው የሆርሙዝ ወሽመጥን በድጋሚ መነጋገሪያ አድርጎታል

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ኢራን እና አሜሪካ ወደ ግጭት መመለሳቸው የሆርሙዝ ወሽመጥን በድጋሚ መነጋገሪያ አድርጎታል

አማራጭ መስመሮች

የሆርሙዝ ወሽመጥ ለኢራን የበላይነት ይሰጣል። የሆርሙዝ ወሽመጥ ኢራን በዓለም አቀፍ የኢነርጂ ገበያ ላይ የበላይነት ስለሚሰጣት የባሕረ ሰላጤው አገራት ነዳጅ ለማስተላለፍ በሌሎች አማራጮች ላይ ከፍተኛ ገንዘብ ያፈስሳሉ።

ከእነዚህ አማራጮች አንደኛው የሳዑዲ አረቢያ 'ኢስት-ዌስት ፓይፕላይን' (ምሥራቅ-ምዕራብ ቧንቧ) ሲሆን፤ ነዳጅ ማስተላለፊያ የቧንቧ መስመሩ 1,200 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። በዚህ መስመር ሳዑዲ በቀይ ባሕር ላይ ከያንቡ የባሕር መዳረሻ ጋር በቀጥታ ትገኛለች።

የተገነባው እንደ አውሮፓውያኑ በ1980ዎቹ በኢራን-ኢራቅ ጦርነት ወቅት ነው።

በጦርነቱ ወቅት ሁለቱም አገራት ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን እና ሌሎችም የንግድ መርከቦችን ዒላማ እያደረጉ ነበር።

በ2019 የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሩ በአንድ ቀን ማጓጓዝ የሚችለው መጠን 7 ሚሊዮን በርሜል ደርሷል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች 406 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የመተላለፊያ አማራጭ ዘርግታለች።

'አቡ ዳቢ ክሩድ ኦይል ፓይፕላይን' የተባለው የነዳጅ ማጓጓዣ የቧንቧ መስመር በአዱ ዳቢ የሚገኘውን የሀብሻን ነዳጅ ማምረቻ በኦማን ባሕር ዳርቻ ከሚገኘው ፉጃይራህ ወደብ ጋር ያስተሳስራል።

ይህ አማራጭ መስመር ከሆርሙዝ ወሽመጥ ውጪ ነዳጅን ለማጓጓዝ ይውላል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ሰዎች ጠቅሶ ፋይናንሽያል ታይምስ እንደዘገበው፤ በዱባይ የሚገኘው የሎጂስቲክስ ኩባንያ ዲፒ ወርልድ፤ በፉጃይራህ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጥ ወደብ ለማቋቋም ዕቅድ ይዟል።

የዱባዩ ጀበል ዓሊ መዳረሻ ላይ ብቻ ጥገኛ ከመሆን ሌሎች አማራጮችን ለመዘርጋት ያለመ ፕሮጀክት ነው። ከሆርሙዝ ወሽመጥ ውጪ ሌሎች መተላለፊያ መስመሮች እንዲኖሩም ያስችላል።

አማራጭ መመስሮችን የሚያሳይ ካርታ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከሆርሙዝ አማራጭ ውጪ አማራጮች ቢኖሩም እንኳን መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ለማድረግ እንደሚያስቸግር ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ ይገልጻል።

አማራጭ መስመሮች በቀን ማጓጓዝ የሚችሉት ከ3.5 እስከ 5.5 ሚሊዮን በርሜል ብቻ መሆኑን የተቋሙ መረጃ ይጠቁማል።

በሆርሙዝ ወሽመጥ ከሚተላለፈው 20 ሚሊዮን በርሜል አንጻር ቁጥሩ አነስተኛ ነው።

በኪንግስ ኮሌጅ ለንደን የዓለም አቀፍ ደኅንነት እና መካከለኛው ምሥራቅ ጥናት ባለሙያ ዴቪድ ቢ ሮበርትስ "ይህ በቂ መጠን አይደለም" ይላሉ።

አማራጭ መንገዶች ውጤታማ እንዳይሆኑ የተለያዩ መሰናክሎች ይገጥሟቸዋል። ለምሳሌ ያንቡ የባሕር መዳረሻ "በዚህ ፍጥነት ይሄንን ያህል ነዳጅ ማስተናገድ አይችልም" ይላሉ ባለሙያው።

ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የዘረጓቸው አማራጭ መስመሮች የጥቃት ዒላማ ሆነዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፤ ኢራን በፉጃይራህ መዳረሻ ላይ ጥቃት ሰንዝራለች ስትል ከስሳለች። በጥቃት ሳቢያ በነዳጅ ማከማቻ ታንከሮች እሳት እንደተነሳ እና የነዳጅ ጭነት እንደተቋረጠም አስታውቃለች።

ያለፈው ሚያዝያ ላይ በነዳጅ ማስተላለፊያ የቧንቧ መስመር በደረሰ ጥቃት ሳቢያ በአንድ ቀን መጓዝ የነበረባቸው 700 ሺህ በርሜሎች መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ተገልጿል።

ሳዑዲ አራምኮ በሦስት ቀናት ውስጥ መተላለፊያው በድጋሚ አገልገሎት እንዲሰጥ ጥገና አድርጓል።

ኢራንም ከሆርሙዝ ወሽመጥ ውጪ ያሉ አማራጮችን ዘርግታለች።

አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የነዳጅ ማስተላለፊያ የቧንቧ መስመር በባሕረ ሰላጤው ጫፍ ከሚገኘው ጎሬህ ተነስቶ ኦማን የሚገኘው ጃስክ የባሕር ጫፍ ይደርሳል።

መተላለፊያው በአንድ ቀን ውስጥ 1 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ያጓጉዛል። ከሆርሙዝ ወሽመጥ ውጪ የኢራንን ነዳጅ ለዓለም አቀፍ ገበያው ያደርሳል።

ማዕቀቦች እና የመሠረተ ልማት ውስንነት የነዳጅ መተላለፊያው በታቀደው መጠን አገልግሎት እንዳይሰጥ ገድበዋል።

ሌሎች የውጭ ንግድ አማራጮች

ሆርሙዝ ወሽመጥን ብቸኛ አማራጭ ከማድረግ ይልቅ ሌሎች የውጭ ንግድ መስመሮችን በመዘርጋት ረገድ ተጠቃሽ የሆነው የነዳጅ ማስተላለፊያ የቧንቧ መስመር ይጠቀሳል።

970 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው መስመር ከሰሜን ኢራቅ ኪርኩክ ግዛት ተነስቶ እስከ የቱርክ የሜድትራኒያን ባሕር መዳረሻ ቼያሀን ይደርሳል።

ለሁለት ዓመት ተኩል ተዘግቶ የቆየው መተላለፊያው በአውሮፓውያኑ መስረከም 2020 በድጋሚ ተከፍቷል።

መጋቢት 2026 ላይ በአንድ ቀን የሚያስተላልፈው ነዳጅ 250 ሺህ በርሜል ደርሷል።

ይህ መተላለፊያ ለኢራን አማራጭ ቢሰጣትም ከአጠቃላይ የወጭ ንግዷ አንጻር ውስን ነው።

ኢራቅ በአንድ ቀን ውስጥ 3.4 ሚሊዮን በርሜል ድፍድር ነዳጅ ኤክስፖርት ታደርጋለች።

ከዚህም 95 በመቶ የሚሆነው በደቡባዊ የአገሪቱ ወደብ ባስራ በኩል አድርጎ በሆርሙዝ ወሽመጥ ያልፋል።

የኪርኩክ-ቼያሀን መስመር በባሕረ ሰላጤው ማለፍ ሳያስፈልገው የኢራቅን ነዳጅ በሶሪያ የሜድትራኒያን ወደብ ያደርሳል።

በሆርሙዝ ወሽመጥ አሜሪካ በፈጸመችው ጥቃት የደረሰ ጉዳት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በሆርሙዝ ወሽመጥ አሜሪካ በፈጸመችው ጥቃት የደረሰ ጉዳት

800 ኪሎ ሜትር የሚደርሰው ይህ መስመር ዝርጋተው የተጠናቀቀው በአውሮፓውያኑ 1952 ነበር።

በኢራን-ኢራቅ ጦርነት ወቅት መስመሩ ተዘግቷል። የቀጣናውን የውጭ ንግድ መስመሮች ለማስፋት በሚል መስመሩን እንደ አዲስ ለመገንባት አሜሪካ፣ ኢራቅ እና ሶሪያ መስማማታቸውን የቅርብ ጊዜ ዘገባዎች ይጠቁማሉ።

'ፎር ሲስ' የተባለ ፕሮጀክት ሜድትራኒያን ባሕር፣ ጥቁር ባሕር፣ ካስፒይን ባሕር እና አረቢያን ባሕረ ሰላጤ በሶሪያ እና በቱርክ በኩል እንዲተሳሰሩ ዕቅድ የወጣበት ነው።

በሚያዝያ 2026 የቱርክ የኢነርጂ ሚኒስትር አልፐራስላን ባይራክታር ባደረጉት ንግግር ኳታር እና ቱርክን የሚያገናኘው የጋዝ መተላለፊያ መስመር ላይ ውይይት እንዲደረግ አሳስበዋል።

ውይይቱ በ2009 የተቋረጠ ሲሆን፤ በአረቢያን ባሕረ ገብ መሬት በኩል ሊዘረጋ የታቀደ መተላለፊያ ነበር።

የኢራቅን ነዳጅ ወደ በቀይ ባሕር ወደሚገኘው የዮርዳኖስ አቃባ ወደብ የሚወስድ የቧንቧ መስመር ለመዘርጋት በአውሮፓውያኑ 1983 ታቅዶ ነበር።

የባስራ-አቃባ መስመር በፖለቲካ ውዝግብ እና የፋይናንስ እጥረት ምክንያት በተደጋጋሚ ሲራዘም ቆይቷል።

የአማራጭ መስመሮች ዝርጋታን የሚደግፉ አካላት እንደሚሉት ኢራን በዓለም አቀፍ የኢነርጂ ፍሰት ላይ ያላትን ጫና የሚያዳክም ነው። የባሕረ ሰላጤው የነዳጅ አቅርቦት እንዳይቆራረጥም ያግዛል።

በሲንጋፖር ኤስ ራጃራትናም የዓለም አቀፍ ጥናት ዩኒቨርስቲ ባለሙያ የሆኑት ሀዜይር ኢዝካኤል ደዙልሂሻም በቅርቡ ባቀረቡት ጥናት እንደገለጹት፤ አዳዲስ መስመሮች ቢዘረጉም እነዚህ መስመሮች ላይ አዲስ ዓይነት ጥገኝነት መፈጠሩ አይቀርም።

"ነዳጅ የማያመርቱ መተላለፊያ አገራት የበለጠ መተላለፊያዎች ላይ ቁጥጥር እንዲኖራቸው የሚያደርጉ መስመሮች ናቸው" ብለዋል።

እንደ ቱርክ ያሉ አገራት የበላይነት ለማግኘት ሊያውሉት እንደሚችሉም ይገልጻሉ።

በኢራን እና ኦማን መካከል የሚገኘው የሆርሙዝ ወሽመጥ ለባሕረ ሰላጤው አገራት ዋነኛ ነዳጅ ማጓጓዣ መስመር ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በኢራን እና ኦማን መካከል የሚገኘው የሆርሙዝ ወሽመጥ ለባሕረ ሰላጤው አገራት ዋነኛ ነዳጅ ማጓጓዣ መስመር ነው

በኢራቅ እና ሶሪያ በኩል የሚያልፉ መስመሮች የደኅንነት ስጋትም ተጋርጦባቸዋል። የቀጣናው አለመረጋጋት፣ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ እና በኃይል አቅርቦት መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ተጠቃሽ ናቸው።

የባሕረ ሰላጤው አገራት የሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ጥገኝነታቸውን ቢቀንሱም ሌላ መስመር መጠቀም ከሚያስከትለው ጂኦፖለቲካዊ ውጥንቅጥ ማምለጥ አይችሉም።

የግብፅ ሱሜድ የቧንቧ መስመር ቀይ ባሕርን ለሜድትራኒያን ጋር ያስተሳስራል። ሱዝ ካናልን ሳይጠቀሙ ወደ አውሮፓ ለመድረስ የሚረዳ ሲሆን በቀን ከ2.5 እስከ 2.8 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ያጓጉዛል።

በቅርቡ የየመን ሁቲ አማጺያን በቀይ ባሕር የንግድ መርከቦች እንዲሁም በባብ ኤል-ማንዳብ ወሽመጥ ላይ ያደረሱት ጥቃት ያለውን ተጋላጭነት ያሳያል።

ግጭቱ ከተነሳ ወዲህ በግብፅ መተላለፊያ የሚንቀሳቀሰው የነዳጅ መጠን ቢጨምርም ለአውሮፓ ከሚያስፈልገው አቅርቦት አንጻር ውስን መሆኑን የዓለም አቀፍ ደኅንነት እና መካከለኛው ምሥራቅ ጥናት ባለሙያ ዴቪድ ቢ ሮበርትስ ይናገራሉ።

አሜሪካ የምትፈጽመውን ጥቃት እስከምትገታ ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥ ዝግ ሆኖ እንደሚቆይ ኢራን አስታውቃለች። በቀጣናው ያለውን የነዳጅ እና ጋዝ የውጭ ንግድ እንደምታውክም አስጠንቅቃለች።

በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኘው ሮያል ዩናይትድ ሰርቪስስ ኢንስቲትዩት የባለሙያዎች ቡድን (ቲንክ ታንክ) የመካከለኛው ምሥራቅ አጥኚ የሆኑት ዶ/ር ኤችኤ ሄልየር እንደሚሉት የባሕረ ሰላጤው አገራት የሆርሙዝ ወሽመጥ ተጠቃሚነታቸውን መቀነስ ይፈልጋሉ።

"የባሕረ ሰላጤው አገራት በተቻለው መጠን ከሆርሙዝ ወሽመጥ ውጭ ወዳሉ አማራጮች ፊታቸውን እያዞሩ ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።

የቀጣናው መንግሥታት ከዚህ ቀደም በነበረው መጠን የሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ መተማመን ስለማይችሉ ለውጭ ንግድ አማራጭ መስመሮች መፈለጋቸውን እንደሚቀጥሉ ይናገራሉ።

ነገር ግን አማራጮች የሆርሙዝ ወሽመጥን ይተካሉ ብለው አያምኑም።

"አንድ መስመርን በአጠቃላይ በሌላ አማራጭ መለወጥ ቀላል አይደለም" ይላሉ።

ነገር ግን አገራት አማራጭ መስመሮች መፈላቸውን በፈለጉ ቁጥር የሆርሙዝ ወሽመጥ አስፈላጊነት "እየቀነሰ" እንደሚሄድ ይገልጻሉ።

የቀጣናው አገራት የእስራኤልንም ይሁን የኢራንን "የበላይነት" እንደማይፈልጉም ያክላሉ።