የአውሮፓ ኅብረት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ውጥረት አሳስቦኛል አለ

የፎቶው ባለመብት, European Union
የአውሮፓ ኅብረት በትግራይ ክልል የተፈጠረው ሰሞነኛ ውጥረት እንዳሳሰበው ገለጸ።
ኅብረቱ ወቅታዊ የክልሉን ሁኔታ በሚመለከት ቅዳሜ ሰኔ 20/ 2018 ዓ. ም. በማኅበራዊ የትስስር ገጹ ባወጣው አጭር መግለጫ የህወሓትን እርምጃ ነቅፏል።
የአውሮፓ ኅብረት በትግራይ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ጥሎ የነበረ ሲሆን፤ ከሁለት ወራት በፊት አቋርጦት የነበረውን የኢትዮጵያ እርዳታ መመለሱን አስታውቋል።
ህወሓት "ትይዩ የክልል ምክር ቤት" ማቋቋሙን እና በክልሉ እያደረገ ያለውን አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ያነሳው ኅብረቱ፤ እርምጃዎቹ በ2015 ዓ. ም. የተፈረመውን የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ስምምነት አንቀጾችን የሚጥሱ ናቸው ብሏል።
የአውሮፓ ኅብረት የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ ለሙሉ እንዲፈጸም በሁለቱም ፈራሚ ወገኖች ማለትም በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል በአስቸኳይ ንግግር እንዲደረግም ጠይቋል።
ኅብረቱ ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን፤ የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ተወካይ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ለማሸማገል የሚያደርጉርን ጥረት ሙሉ ለሙሉ እንደግፋለን ብሏል።
በምርጫ ቦርድ ሕጋዊ እውቅናው የተነሳው ህወሓት በፊደራል መንግሥቱ የተሾመውን ጊዜያዊ አስተዳደር በማስወገድ ከጦርነቱ በፊት በነበረው ምርጫ ያሸነፈውን ምክር ቤት ከመለሰ ወራቶች ተቆጥረዋል።
"የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ" ባለፈው ሚያዝያ ከስድስት ዓመት በፊት "የተመረጠው የትግራይ መንግሥት ምክር ቤት ወደ ሥራ" እንዲመለስ መወሰኑንን ተከትሎ፤ ይህ ምክር ቤት የቀድሞውን የክልሉን ርዕሰ መስተዳደር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን ዳግም ፕሬዝዳንት አድርጎ መርጧል።
"መፈንቅለ መንግሥት" አድርጎ ሥልጣን ተቆጣጥሯል የሚባለው ህወሓት የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እያደረገ እንደሆነ ተዘግቧል።
በቅርቡ "ለትግራይ ሕዝብ ኅልውና እና ደኅንነትን ለማረጋገጥ" በሚል ያወጣው አወዛጋቢ ሕግ የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎትን የሚፈቅድ ነው።
የክልሉ "ምክር ቤት" አፈ ጉባኤ ምሕረት በርሀ በዚህ ሳምንት በጻፉት ደብዳቤ የሕጉ ተፈጻሚነት በአስቸኳይ እንዲጀምር መመሪያ አስተላልፈዋል።
አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላው ከፖለቲከኞች እና ከሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን፤ ሂውማን ራይትስ ዋች ከሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ሕጉን "ጨቋኝ" ብሎታል።
ባለፈው ግንቦት በህወሓት የተያዘውን የክልሉን መንግሥት "አስወግዳለሁ" ያለ እና ራሱን "የትግራይ የሰላም እና የለውጥ ምክር ቤት" የሚል ቡድን በአዲስ አበባ ተመሥርቷል።
አሜሪካ በዚህ ወር በኢትዮጵያ ያለውን ሰላም በማናጋት ውስጥ ተሳታፊ ናቸው ባለቻቸው አክራሪ የህወሓት አባላት እና ቤተሰቦቻቸው ላይ የቪዛ ክልከላ መጣሏን አስታውቃለች።
ህወሓት የአሜሪካን የቪዛ ክልከላ "ሚዛናዊ ያልሆነ" ሲል አውግዟል። የአሜሪካ እርምጃ የትግራይን እውነታ እንደማያንጸባርቅ እና የፌደራል መንግሥቱን "ተጠያቂ ያላደረገ" መሆኑን በመጥቀስም ኮንኗል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ አርብ ሰኔ 19/2018 ዓ. ም. ባወጣው አጭር መግለጫ፤ በትግራይ የሰላም ሂደትን "እያደናቀፉ" ናቸው ያላቸው እና በስም ያልጠቀሳቸው አካላት ለውይይት ጥረቶች ትብብር እንዲያደርጉ አሳስቧል።
የፖለቲካ እና የሲቪል ማኅበረሰብ መሪዎች በፖለቲካ ውይይት ውስጥ መሳተፍ እና የፕሪቶሪያውን ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ሙሉ በሙሉ መተግበር እንዳለባቸውም አሳስቧል።















